Tuesday, March 26, 2013

ሰውና ተግዳሮቱ


                   ከባድ ነው የሰው ልጅ በራሱ ጥላ መበርገግ ሲጀምር! አስቸጋሪ ነው የሰው ልጅ በንግግሩ መልሶ ሲሸማቀቅ! ይልቁን ደግሞ ውድመት ነው የሰው ልጅ ከገዛ ልቦናው ጋር ሲቃቃርና ሲተዛዘብ! ቴዎድሮስ ታደሰ 1999 ዓ.ም ካወጣው አልበም ውስጥ ዝምታ የሚለው ዘፈኑ ላይ ሁሌም ስሜቴን የሚይዝ ስንኝ አለ "አቤቱ! የሰው ልጅ ፅናቱ! ትዕግስቱ ብርታቱ!..." እያለ በጥልቅ ስሜትና የሙዚቃ ቅንብር ድምፃዊው ያንጎራጉራል። የዚህ ዘፈን ገጣሚ በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ አንዳች የገባው ነገር ያለ ይመስላል በርግጠኛነት መናገር የምችለው ግን እውነትም ሰው ብርቱ ነው አንዳንዴ ከፈጣሪው ጋር እየተጣላ፣አንዳንዴ ከተፈጥሮ ጋር እየተጋጨ፣ሌላ ጊዜም ከራሱና ከማህበረሰቡ ጋር እየተዋጋ ቆሞ መሄድ መቻሉ ፍፁም የሚያስደንቅ ክስተት ነው። 
ሰው ለምን ከፈጣሪው ጋር ይጣላል?
ከመንፈሳዊ እይታ አንፃር ፈጣሪን ተመርኩዘው የተፈጠሩ አራት ዓይነት ቡድኖች መኖራቸው የታወቀ ነው እነሱም፡-
 1. ቴኢስት (በፈጣሪ መኖር የሚያምኑ) 2. ኤቲስት (ፈጣሪ የለም የሚሉ) 3. አግኖስቲክ (ሊኖርም ላይኖርም ይችላል አያገባንም የሚሉ) 4.ግኖስቲክ (ፈጣሪ ዩኒቨርሱ ነው አለ የለም አይሉትም ይኖሩታል፣ይዋሀዱታል እንጂ የሚሉ) ናቸው ምሁራን የትኛውም ሰው ከእነዚህ ከአራቱ ውጭ ሊሆን አይችልም ይላሉ ከእነዚህ ዘርፎች ውስጥ ቴኢስቶች በፈጣሪ ህልውና ስለሚያምኑ ከእርሱ የሚፈልጉትን ባጡ ጊዜ ይሞግቱታል ይከሱታል "እኔ እንዲህ ስሆን ዝም ያልክ እውነት የለህማ!" እያሉ ፀሎታቸውን እስኪሰማ ያማርሩታል! መልስ ካጡም ገሚሱ እንዳኮረፉ በትዕግስት ይጠብቁታል ገሚሱ ይተውታል የቀሩት ወደ ኤቲስትነት ጎራ ዘንበል ሊሉም ይችላሉ ዋናው ነገር ግን የሰው ልጅ እንደ አማኝ ከፈጣሪው ጋር ሊታገልና ሊጣላ እንደሚችል በተለያዩ ሀይማኖታዊ መዛግብት ውስጥ ተመዝግቦ ማግኜታችን ነው።
 ሰው ለምን ከተፈጥሮ ጋር ይጣላል? 
የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውስጥ እንደ አንድ ፍጥረት ቢሆንም የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ተፈጥሮን መልሶ በማፍረስና በመገንባት፣ በመግዛትና በማስተዳደር ለራሱ እንድትመች አድርጎ ሲጠቀምባት ለመኖሩ ከዘመናት በፊት የነበሩና በአርኪዎለጅ ጥናት የተገኙ ስንክሳሮችና ሌሎች ተያያዥ ቁስ አካላት ይጠቁማሉ የዚያኑ ያህል ደግሞ ልክ እንደ የአየር መዛባት፣የውሀ መጥለቅለቅ፣መብረቅና ሰደድ እሳትን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች መልሰው የሰው ልጅን ለእንግልት ለስደትና ለሞት ሲዳርጉት እንደኖሩ አሌ የማይሉት እውነት ነው በዚህ ጊዜ ሰው የኖረበትን አካባቢ ረግሞ ወደሌላ መልክዓ ምድር ሄዶ ይሰፍራል ሌላው ሰብዓዊ ፍጡር ከተፈጥሮ ጋር የሚጣላበት መንገድ እንደሚታወቀው ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች በሚለቁት የተበከለ ጋዝ ምክንያት ተፈጥሮ አፀፌታዋን የምትመልስበት መንገድ ነው በርግጥ ይሄኛውንም የአረንጓዴ ፖሊሲ በማርቀቅ ጠቡን የማርገብ እድል አለ ከተፈጥሮ ተጣልቶ ከተፈጥሮ ጋር በመታረቅ።

ሰው ለምን ከማህበረሰብ ጋር ይጣላል? 

ይሄኛው የሰው ልጅ ከራሱ መንጋ ጋር የሚያደርገው ተጋድሎ የሚፈጠረው ያስማማኛል ብሎ ባረቀቀው በራሱ ህግ፣ስርዓት፣ደንብ፣ ባህልና ወግ መሆኑ አስገራሚ ነው ከእንስሳት ውስጥ ከራሱ መንጋ ጋር የሚጣላ የሰው ልጅ ብቻ ነው ያውም የሚያስብ እንስሳ ሆኖ! በአንድ አካባቢ የሚያግባቡ ልማዶቹ በሌላኛው መንደር ነውርና አስፀያፊ ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ ብዙ ነው እዚህ ጋ ሰው የሚለውን
ስም እንደ ግለሰብ እየተጠቀምኩ እንደሆነ ልብ ይሏል። ሰው ከቤተሰቡ ከአካባቢውና ከማህበረሰቡ ጋር የሚፈጥራቸው መስተጋብሮች መልካም እንዲሆኑ የሚፈልገውን ያህል ጥቅሙ ሲነካበት የገዛ ወገኖቹን በመተው እልፍ ሲል የማሴርና የማጥቃት ዝንባሌ ሊታይበትም ይችላል ወግና ስርዓት ከሚፈጥረው አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ባሻገር የሰው ልጅ በአካላዊ ጉዳትና በስነ ልቦናዊ እክል በዙሪያው ካሉት ሌሎች ሰብዓዊ ፍጡራን ጋር ሊጋጭ ብሎም በህይወትና በንብረት ላይ ውድመት ሲፈጥር ይታያል

ሰው ለምን ከገዛ ራሱ ጋር ይጣላል?
ሰው እንዳሰበው መጠን፣እንደአቅሙ መጠን፣እንደሚገባው መጠን መኖር ሳይችል ሲቀር ከራሱ ጋር ሊጣላ ይችላል ደግሞ ሰው ያለውን ሙሉ ግብዓት ተጠቅሞ ከተሳካለትና ክብርና ዝና ካተረፈ በኋላም በድንገተኛ እክል የነበረውን አሴት እንዲሁም በዙሪያው ያለውን ድጋፍ ሲያጣ ማንነቱን ሊጠላ ብሎም ራሱን እስከማጥፋት ሊደርስ ይችላል። ከዚህ ሀሳብ ጋር በተያያዘ ከኧርቪንግ ዋላስ "የደፈረሰ እንባ" መፅሀፍ መገባደጃ ላይ እንዲህ የሚል ቃል ሰፍሮ ይገኛል "በዚች ዓለም ማጣት የሰው ልጆችን ያሳዝናል ከዚህ የሚልቀው ግን አግኝቶ ማጣት ነው"። ሰዎች ለመኖር መብላት ትተው ለመብላት ሲኖሩም ይሰላቹና ተስፋ ይቆርጣሉ ሰዎች ለሌሎች የመኖር ዝንባሌን ከተፈጥሮ እንደተቸሩት የስነ ልቦና ባለሞያዎች ደጋግመው የሚነግሩን እውነት ከመሆኑ አንፃር መሰረታዊ ፍላጎታቸው ቢሟላም ለሰው ልጅ የሚበጅ ነገር አላደረግንም ብለውም ነፍሳቸውን ሊፀየፏት ይችላሉ በዋነነት ግን የሰው ልጅ ከገዛ ራሱ ጋር የሚጣላው ማህበረሰቡም ሆነ የገዛ ህሊናው የሚያወግዘውን ድርጊት ፈፅሞ በሚገኝበት ጊዜ ነው ያም ለምሳሌ አባት በገዛ ሴት ልጁ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲፈፅም፣እናት ከአቅም በላይ በሆነ ችግርም ቢሆን የወለደችውን የአራስ ቤት ልጇን ስትጥል፣የሀገር መሪ በርካሽ ጥቅም ዜጎቹን ለባዕድ ባርነት አሳልፎ ሲሰጥና በሌሎች መሰል አስነዋሪ ጉዳዮች የሰው ልጅ ሲሳተፍ ቆይቶ ወደ አዕምሮው ሲመለስ ሞቱን አጥብቆ ይመኛታል። 

መፍትሄ ይኖር ይሆን?
(የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ሳይንሳዊ መላምቶችን ጠቅሶ ሳይሆን በራሱ መረዳት ከገባው ነገር ተነስቶ መፍትሄ የሚለውን ለውይይት ያቀርባል)
             የሰው ልጅ ከፈጣሪ፣ከተፈጥሮ፣ከማህበረሰብና ከገዛ ራሱ ጋር ያለበትን ተግዳሮት በጥቂቱም ቢሆን ከላይ አይተናል። ሰው ለመንፈሳዊና አካላዊ ማንነቱ ሀላፊነት መውሰድ አለበት የሚል እምነት አለኝ ፈጣሪ ያደርግልኛል ካለ በእምነት በመጠበቁ ለሚደርስበት ነገር ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል። እኔ የራሴ አምላክ ነኝ የሚል ኢ አማኝ ከሆነም ለሚደርስበት የትኛውም ከባድ ሸክም ራሱን ይፈትን። ነገር ግን በደስታው ጊዜ ሀላፊነቱን ወስዶ ሲቸገር ያልነበረ ጌታውን ፈልጎ የሚወቅስ ከሆነ ያ ሰው ምክንያታዊ አይደለም ማለት ነው። ሰው ከተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር የሚፈጠሩ አሉታዊ ግብረመልሶችም እንዲሁ "መስጠትና መቀበል" በሚለው ህግ ሊዳኙ ይገባል እንጅ ተፈጥሮን የማራቆት የትኛውም ቅንቅስቃሴ ራስን ማራቆት መሆኑን ማንም ለማንም አይነግረውም። በአንፃሩ ከማህበረሰብ ጋር ያለው ሰብዓዊ ግጭትም የሚፈታው ህግጋትንና ስርዓትን በመደርደር የሚመጣ ሳይሆን የገዛ ተፈጥሯችንን በመረዳት፣በልቦናችን የተፃፈውን ህግ በማንበብና ፍቅርን በመላበስ የሚፈታ ይመስለኛል። በዋናነት ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ያለው ማለት ሰው ከፈጣሪ፣ከተፈጥሮና ከማህበረሰብ ጋር የሚገጥመው ተግዳሮት ከባድ የሆነበት ምክንያት ከገዛ ራሱ ጋር መስማማት ስላልቻለ ነው ሰው ሰውነቱን የምሩም አምኖ ቢቀበል ከእንስሳት መንጋ በተሻለ እንጅ ባነሰ ሁኔታ እርስ በራሱ ሊጋጭና ሊባላ ከቶውኑ ባልቻለም ነበር። የሚሆነው ነገር መሆን ስላለበት ይሆናል ስንል ህይወት እንድትመራን ፈቅደናል አንዳንዱ ነገር በእኛ ስንፍና ሳይሆን ቀርቷል ስንል ደግሞ ህይወትን መስመር ልናስይዛት ይገባል። ያኔ ለውድቀታችንም ለስኬታችን ሀላፊነት ስለምንወስድ ፈፅሞ ከራሳችንም ሆነ በዙሪያችን ካሉ ኃይላት ጋር ልንጣላ አንችልም ከዩኒቨርሱ ጋር በስምምነት፣በፍቅርና በተድላ አብረን እንፈሳለን እንጅ።ሻሎም።

No comments:

Post a Comment