ሰው ትናንቱን መርሳት፣ነገውን መተውና ዛሬውን መውረስ ሲችል እውነተኛ አቅሙን መጠቀም ይጀምራል፤ሰው ጠላቱን መማር፣ሸሪኩን ማክበርና ወዳጁን ማፍቀር ሲችል ግማሽ አቅሙን ይጠቀማል፤ሰው ስንፍናውን ሲሽር፣ዕውቀቱን ሲመነዝርና ጥበቡን ሲኖር ከስነ-ፍጥረቱ የሚጠበቀውን ፍፁምና ሊሞላ ተቃርቧል፤ሰው ስለሰው ሲያስብ፣ስለዓለማቱ ሁሉ ሲገደውና ስለፍጥረት ፈጣሪ ሲዘምር ግን ያኔ ፍፁም አቅሙን ተጠቅሟል! ፍፁም ሆኗል! አዎ ይህን ማድረግ ይቻላል ከዛሬ አሁን ከአሁንም በዚች ቅፅበት ለራሳችን እንዲህ ብለን ቃል ብንገባስ?
“ከአቅም በታች መኖር አልፈልግም! ‘አትችልም፣አይሆንልህም!’ የሚሉኝን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ድምፆች ካሁን ጀምሮ ቦታ አልሰጣቸውም! እኔ ዓለምን እንዳበጃት፣እንድገዛትና እንድባረክባት ተፈጥሬያለሁ! አቅም እንዳለኝ ህሊናየ ልቦናየና አካሌ ይመሰክሩልኛል! እንግዲህ የፈረሰውን አድሳለሁ! የተነቀለውን እተክላለሁ! የበሰበሰውን አስወግዳለሁ! ሰው ሆኜ የተፈጠርኩት እንድማር መሆኑ ይገባኛል ስለዚህም ከተፈጥሮ የሚመጣውን የትኛውንም ዕውቀት በንቃት እቀስማለሁ! የተፈጥሮን ሚዛን ለመጠበቅ ከህይወታዊና ህይወት አልባ ፍጥረታት ጋር በተጓዳኝ ቆሜ በወዳጅነት አብሬ እሰራለሁ! እያንዳንዷን የኑሮ ቅንጣት ጊዜ እንደ ልዩ ስጦታ ቆጥሬ በተድላ ስመላለስ የኋላየን ትቼ ወደፊት እየተዘረጋሁ እንደሆነ ይሰማኛል። ሁሌም ሰው ሆኜ በመፈጠሬ ደስ ይለኛል! እንስሳትን አፈቅራለሁ! እፅዋትን አደንቃለሁ! በተራመድኩ ቁጥር፣በተመገብኩ ቁጥር፣በሰራሁኝ ቁጥር ከአሁኔ ጋር ነኝና ፍስሃ በህዋሳቶቼ ሁሉ ይመላል! ፈጣሪ እንዴት ያለውን እውነተኛ ሰላም እንደሰጠኝ በማወቄ ከእንግዲህ ለአምላኬ የሚፈነቅል የምስጋና መዝሙር ነፍሴ ትቀኛለች! ምላሴም እንደቀደሙት ወገኖቿ በበገና፣በድቤና በአታሞ ታጅባ ለፍጥረት ሁሉ ገዥ፣ለሩህሩህና ቸር አምላክ ታዜማለች! ታሸበሽባለች! ትሰጣለች! አሜን! አሜን! አሜን! እልልልልልልልልልልልልልልልል...
No comments:
Post a Comment