ደረጀ፣ደረጃ፣አደራጀ፣ተደራጀ፣ድርጅት፣መደራጃ፣መደራጀት፣አደራጅ፣ተደራጅ... የሰው ልጅ ደረጃው ብዙ ነው ሊፍት ከሌላቸው ቁስ-አካላዊ የኮንደሚንየሞቻችን ፈታኝ ደረጃዎች ጀምሮ እስከ መንፈሳዊው የያዕቆብ መሰላል ድረስ የሰው ልጅ በብዙ መዉጫና መውረጃዎች ላይ ተመላልሷል፤እድሜ ይስጠው እንጅ ወደፊትም ይመላለሳል። ደግሞ የሰው ልጅ ደረጃው ብዙ ነው ምግብ፣ልብስና መጠለያ ከሌላቸው ምስኪን ወገኖች ጀምሮ እስከ ሰው እስከሆነው አምላክ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ድረስ የሰው ልጅ በእልፍ ድንግዝግዝ እና አብርሆት ላይ ታች ብሏል፤ይላልም። ምንም እንኳ “መሃሉ አይነገርም” የሚል መጽሐፍ አንብቤ የወደድኩ ብሆንም የኔ የጽሁፍ ሃሳብ ግን ከእነዚህ ሁለት ፅንፎች መሃል ሲዋልል ታገኙታላቹህ።
ያ ደሃ፣እገሌ፣ እንቶኔ፣ማንትሴ፣ደሳሳ ቤት፣... አቶ፣እሳቸው፣እኒያ፣እኒህ፣የተከበሩ፣ክቡር፣ታላቁ፣ባለሀብቱ፣ፎቅ ቤት... ሳላውቀው ቃላት ለቀማ ውስጥ የገባሁ ቢመስለኝም ግን በቃላት ውስጥ አንዳች ነገር መኖሩ ያም ብዙውን ጊዜ የአንድን ግለሰብ ደረጃ የሚገልፅ ሆኖ ባገኜው የአማርኛ ቋንቋ መምህር ይመስል በየፊደላቱ ሳይቀር ተመሰጥኩኝ። የሰው ልጅ ለምን ለነገሮች መለኪያ ማብጀቱ ሳያንስ ራሱን መለካት ፈለገ? በማንትሴ ሰቀላ እና በእኒያ “ጂፕሰም” ቤቶች መካከል ያለው ርቀት የሚታይና የሚጨበጥ ስለሆነ ልተወውና ግን በ”ማንትሴ” የንቀት እና በ”እኒያ” የክብር መጠሪያዎች መካከል ያለው ርቀት ምን ያህል ነው? ሲጀመርስ ርቀት አለ ወይ? ሰብአዊነት መነሻ እና መዳረሻችን ከሆነ ማለቴ ነው።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያሉ እንደ STATUS, LOW CLASS, HIGH CLASS, STANDARD አይነትና የመሳሰሉት ቃላቶች ለኔ ከፋይዳቸው ይልቅ ወለፈንዳቸው ጎልቶ ይታየኛል። ወዳጆቼ ቃላት ካቅማቸው በላይ ብዙ ነገር አጭቀው መያዛቸውን ማወቅ እንደመገለጥ ነው የሆነብኝ (ሳቅ) እስኪ አስቡት ኑሮ የለየውን ላይኛውን እና ታችኛውን መደብ እንደገና ሃብታምና ደሃ ብሎ መለየት ምን ይባላል? ለሰራነው ታላቅ ስህተት ተገቢ እውቅና መስጠት ይሆንብኛል አንዳንዴ ይሄ ከመግባቢያ በላይ የሆነውና መንግስትና አፈቀላጤዎቹ የሚጠቀሙበት ቋንቋ የሚሉት ነገር! ለምሳሌ መደራጀት የሚለው ቃል ሲያግባባን መሰባሰብ፣አብሮ መስራት፣መተጋገዝ...እና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን አወንታዊ ትርጓሜዎች ጠቅልሎ ይይዛል። መደራጀት ይሉት ቃል ግራ ሲያጋባን ግን አይጣል ነው፡- ማሰባሰብ ለልማት፣ማሰባሰብ ለፖለቲካ፣ ማሰባሰብ ለጥፋት እና ሌሎች አሉታዊ ትርጓሜዎች የሚኖሩት ይመስለኛል፤አውዳዊ ፍችውን ግን “እነሱ” ይወቁት እንጅ ለኔስ ይጠጥርብኛል።
የሰው ልጅ እንስሳነቱ
እዚያ ቤት በስርዓት ተቀምጧል፣
በስርዓት እያነሳ
በስርዓት አጥንቱን ይግጣል።
የሰው ልጅ ሰውነቱ
እዚያ “ጥግ” በዝርግፉ ተለጥጧል፣
በተርታው ተጋድሞ
ዝርግፍ ህልሙን ያላምጣል።
የሚል ግጥም እንድፅፍ አስገድዶኝ ሁሉ ነበር ይህ ሰው ሰራሽ STATUS የነካኝ ቢመስለኝ ተሶርፌ፣ያረከሰኝ ቢመስለኝ ተፀይፌ! የኔ ነገር አሁንም ግጥም አደረኩት ስሜቴን (ሳቅ)። ይሁን ወደ ሃሳቤ ልመለስ። “ደረጃና አደራጅ” በሚለው ቃል ውስጥ እግዚአብሄር (ልዕለ ተፈጥሮ)፣ተፈጥሮ፣መንግስትና ህብረተሰብ የሚባሉ አበይትና ንዑስ እርከኖች አሉ እንበል። እግዜርም በተፈጥሮ በኩል አብይ ነውና ንዑስ ህብረተሰብን ሲያደራጅ ራሱ ደረጃ ራሱ አደራጅ ሆኖ ነው። ምክንያቱም እግዜር “ፈጣሪ” ነዋ! እኔ ያልገባኝ ህብረተሰብ አብይ በሚሆንበት ዘርፍ ንዑስ መንግስት እንዴት ብሎ ነው ራሱ “ደረጃና አደራጅ” የሚሆነው? በየትኛው አካሄድ ነው ዋናው ህዝብ በማይገባው መስፈርት ተዘግኖ የሚሰፈር የእንደራሴ እህል የሆነው? ለመስፈርም እኮ መስፈሪያ ያስፈልጋል! ተሰፍሮ ማወቅንም ይጠይቃል! የእግዚአብሄር ከሆነው መንፈሳዊ እውነት በቀር በዚህ ምድር እየሰራ ያለ አመክንዮ ይህ ነው! መንግስት ለማደራጀት የሚሆን ደረጃ አለው ወይ? ማለት ገንዘብና ዕውቀት እኩል የማበደር ዓቅም አይታቹህበታል ወይ? ዝም ብሎ ደረጃ ላይ “ቂብ” ይባላል ወይ? ወይ? ወይ? (መንግስት በዚህ ፅሁፍ ካላሰረኝ ዋጋ የለኝም (ረጅም ሰላማዊ ሳቅ) ሎል)
ወደ እኛ ልመለስ፡- እኛስ ሲያደራጁን የመደራጀት ጊዜያዊ ብልጠት ብቻ ነው ያለን ወይስ የደረጃ ፅንሰ-ሃሳብ ገብቶናል? በመደራጀት ውስጥ ያለው ስረወ-ቃል “ደረጀ” እና ርቢው “ደረጃ” ማደግን ከፍ ማለትን እኮ መሰለኝ የሚጠቁሙን!? ስለዚህ በየትኛውም ድርጅት ውስጥ ያለ መደራጀት መደርጀትን ተልሞ የሚንቀሳቀስ ነው። ይህ ማለት መጀመሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ በእጅጉ ያስፈልጋል ቀጥሎ ሃገራዊ ስሜት እንዳውም ቢቻል አለም-አቀፋዊ ስሜት ይጠበቃል፤እንግዲህ ከእነዚህ ከሁለት ነገሮች እውናዊነት በኋላ ነው ገንዘብ የሚያመጣው የለውጥ ደረጃ የሚታየው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ያማረ ቤቱን ብቻ አይደለም፤የራሱ አካላዊ ቤትም አለውና! ምክንያቱም የሰው ልጅ ያማረ ሱፉና ያነቀው ከረባቱ ብቻ አይደለም፤የራሱ መንፈሳዊ ልብስና የሚቆነጥጠው አዕምሮም አለውና! ምክንያቱም የሰው ልጅ በባንክ ያከማቸው ብሩን ብቻ አይደለም፤በማይታየው ዓለም ነፍሱ ነፍሱን የምትወቅስበት ያከማቸው ስራ አለና!(በቡዲሂስት እምነት ተከታዮች ዘንድ “አካሽክ ሪከርድ” በላይኛው ዓለም ሰዎች የሚፈፅሙት ሁሉ የሚመዘገብበት የትውስታ ማዕከል ሲሆን ነፍስ ከስጋዋ ስትለይ ወደዚህ ቦታ በመሄድ የሰራችውን በማየት ራሷ በራሷ ትፈርዳለች ይላሉ።)
በዚህ ሃሳብ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል ግን ርዕሱ አንዴ ወደ ፍልስፍናው ዘውግ አንዴ ወደ ፖለቲካው ዘውግ የማንሸራተት ባህሪ አለው ወይ እኔ እንደዛ ሆኛለሁ። አንዳንድ ቦታ ላይ የሰው ልጅ ሰው ነው ደረጃ አይደለም እያልኩ ነበር፤ እያሰብኩ ነበር ማለት ነው። አንዳንድ ቦታ ላይ የሰው ልጅ ራሱ ይደራጃል እንጅ አያደራጁትም እያልኩ ነበር መሰለኝ፤ያለ ኩላሊት ”ስቦተልክ” መሆኑ ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? አለ ሃዋርያው ጳውሎስ ወደ...ሰዎች በፃፈ ጊዜ! እውነት ብሏል! እኔስ ምን እላለሁ? አለማለትም ማለት ነው ማለትም ያለማለትን ያህል ነውና! ምክንያቱም መኖር ባይገባቸውም “ደረጃና አደራጅ” አሉና!.............................ሻሎም!
No comments:
Post a Comment